የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው
ሸገር ከተማ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ገለፀ።
በመላ አገሪቱ "በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ" የመትከል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ተጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎችም በነቂስ በመውጣት አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተጀመረውን ይህን መርሃ ግብር መነሻ በማድረግ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት እንዲሁም የሸገር ከተማ የመና አብቹ ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ሰራተኞችና ነዋሪዎች በአካዳሚው ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ርዕሰ አካዳሚ ወንድዬ ለገሰ (ዶ/ር) ፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር ፣ለቀጣይ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ የሚያስችል ነው ።
አካዳሚው በአሁኑ ወቅት ብቁ አመራር የማፍራት ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።
መርሃ ግብሩ ኢኮኖሚውን ከመደገፍና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ እንዳለውም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ በበኩላቸው፣ ካፒታል ገበያው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ፀድቀው ለታለመለት አላማ እንዲውሉ ይሰራል ነው ያሉት።
በሀገሪቱ ዘላቂ ብልጽግናን ለማምጣት በኢኮኖሚ፣ በአረንጓዴ ልማት እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩል የሚሰሩ ሥራዎች በአንድነትና በተቀናጀ መንገድ ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል።
በሸገር ከተማ የመና አቢቹ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለሚ ረጋሳ በበኩላቸው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሸገር ከተማ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን መመናመንን መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ተሰደው የነበሩ የዱር እንስሳትን ወደ ቦታቸው ለመመለስ ያስቻለ ሲሆን ደርቀው የነበሩ ምንጮችንም ለማጎልበት ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተማዋን ለማስዋብ በተከናወኑ በርካታ ስራዎች ውስጥ ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ያሳየውን ከፍተኛ ተሳትፎን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።