ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ መግባባትን ከመትከል ጋር የተቆራኘ ተምሳሌታዊ ልማት ነው - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ መግባባትን ከመትከል ጋር የተቆራኘ ተምሳሌታዊ ልማት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ግብ ከማለዳው 12፡00 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተመካካሪዎችም ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሀሳብና መግባባትን የመትከሉ ሂደት ለዴሞክራሲ ስርዓት ትልቅ እርሾ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች፣ አርብቶ አደሮች፣ አርሶ አደሮችና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በተወከሉበት ደረጃ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ አጠቃላይ ሂደት ሀሳብን፣ መግባባትንና መነጋገርን የመትከል ሂደት መሆኑንም ፕሮፌሰር መስፍን አስታውቀዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በምክክሩ ወደ መግባባት የሚወስዱ ሀሳቦችን በመነጋገር እየተከልን ነው ብለዋል።

ማዳመጥንም እያሰፋን እንገኛለን ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ይህ ሂደት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መነሻነት ትልቅ እርሾ እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መሳሪያን አስቀምጦ ከመመካከር፣ ሰላምና ልማትን ከማምጣት እንዲሁም ህዝቦችን በማቀራረብ አንድነትና ብዝሃነትን ከማጠናከር አንጻር የምክክሩ ሂደት ከችግኝ ተከላው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ተምሳሌታዊ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል።

በዕለቱ የተሳተፉት 4ሺህ ተመካካሪዎች ችግኝ የተከሉት ለ130 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝቦች መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ቀኑ ለሀገሪቱ ህዝቦች ትልቅና ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም