በሸገር ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ስራዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ስራዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል
ሸገር፤ ሐምሌ 27/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ተግባራት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) አስታወቁ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በሚካሄደው ዘመቻ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብም በሰፊው በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
በመርሃግብሩ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተው ችግኝ በመትከል ላይ ናቸው።
ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በወቅቱ፤ በሸገር ከተማ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እየተሰራ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ የተፈጥሮ ሀብት ውድመትን ለመከላከል፣ የደን ሽፋን ለማሳደግና የአየር ንብረት ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብርም ለደን፣ ለውበት፣ ለምግብነት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በችግኝ ተከላው ተሳታፊ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል የገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ለሊሴ ተስፋዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ለሦስተኛ ጊዜ በችግኝ ተከላ ዘመቻው መሳተፋቸውን በመግለጽ፣ ለወደፊቱ ለትውልዱ ምቹ ሀገር ለማስተላለፍ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አክለዋል።
ወጣት ተስፋዬ ዴሲሳ እንዳለው፣ ዕፅዋት ለሰው እና ለእንስሳት ጤና አስፈላጊ በመሆናቸው በችግኝ ተከላው በንቃት መሳተፉንና መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተከታታይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም አብራርቷል።
አረንጓዴ ምድርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ዛሬ ችግኝ መትከል ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ለችግኞቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግም አረጋግጧል።
ሕፃን ፍሮምሳ ፍቅረማርያም በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በችግኝ ተከላ ላይ መሳተፉን ገልጾ፣ ችግኝ መትከል ንጹህ አየር ከማግኘት ባለፈ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልም ነው ብሏል።