ቀጥታ፡

ዛሬ የተከልናቸው የፍራፍሬ ችግኞች አማራጭ ገቢ የሚያስገኙልን ናቸው

 አዋሽ መልካሳ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦በዛሬው ዕለት በአንድ ጀምበር በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃግብር የተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች፣ ከመደበኛው ግብርና ጎን ለጎን ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑ በአዋሽ መልካሳ የመርሃግብሩ ተሳታፊዎች ገለጹ።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ቱጂ አብዶ፣ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ለትውልድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚረዳ የጠቆሙት አቶ ቱጂ፣ ሥራው ለራሳችን፣ ለክልላችንም ሆነ ለሀገራችን የሚጠቅም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የፍራፍሬ ችግኝ ተከላው ለነገው ትውልድ  ስንቅ እንደሚሆን አንስተው፤ ችግኞቹን ከመትከል ባለፈ ተንከባክበው ለፍሬ እንደሚያበቋቸው ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አመለወርቅ አያሌው በበኩላቸው፣ ዛሬ  የተከሉት ችግኝ ለነገው ትውልድ ተስፋ እንዲሆን በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ አመለወርቅ አክለውም በየዓመቱ መርሃ ግብሩ ላይ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፣ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄዱት የተከላ መርሃ ግብሮች በመሳተፍ የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ውጤታማ ማድረግ መቻላቸውንም ገልጸዋል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሳይንሳዊ ይዘቱን ተከትሎ እንዲከናወን በተሰጠው ግንዛቤ መሠረት እየተገበሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ አብደላ ከድር ናቸው።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ መተላለፉንም ገልጸዋል።

በተለይም የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ፣ የሎሚ፣ የብርቱካንና የዘይቱን ችግኞች በስፋት መተከላቸውን ገልጸው፤ ይህም አርሶ አደሩ ከመደበኛ የሰብል ልማት ጎን ለጎን ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በምግብ ራስን ለመቻልና ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ቁልፍ አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በ100 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር መተከላቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋምና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ችግኞቹ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻልና ገቢውን ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አለሙ፤ ይህም አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር በሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ በስፋት እንዲሰማራ በማድረግ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ፣ የሎሚና የብርቱካን ምርጥ ዘሮችን ከውጭ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጋቸውን አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም