በሸገር ከተማ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ስራዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ስራዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል
ሸገር፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ተግባራት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) አስታወቁ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በሚካሄደው ዘመቻ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብም በሰፊው በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
በመርሃግብሩ ላይ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የከተማዋ አስተዳደር አመራሮች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተው ችግኝ በመትከል ላይ ናቸው።
ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በወቅቱ፤ በሸገር ከተማ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እየተሰራ ያለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ የተፈጥሮ ሀብት ውድመትን ለመከላከል፣ የደን ሽፋን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በከተማዋ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተገኙትን እነዚህን ስኬቶች የበለጠ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራም ከንቲባው ተናግረዋል።
በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ለደንነት፣ ለውበት፣ ለምግብነት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በችግኝ ተከላው ተሳታፊ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል የገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ለሊሴ ተስፋዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ለሦስተኛ ጊዜ በችግኝ ተከላው ዘመቻ ላይ መሳተፋቸውን በመግለጽ፣ ለወደፊቱ ለትውልዱ ምቹ ሀገር ለማስተላለፍ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አክለዋል።
ወጣት ተስፋዬ ዴሲሳ እንዳለው፣ ዕፅዋት ለሰው እና ለእንስሳት ጤና አስፈላጊ በመሆናቸው በችግኝ ተከላው በንቃት እንዲሳተፍ እንዳነቃቃው ተናግሯል።
የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተከታታይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም አብራርቷል።
አረንጓዴ ምድርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ዛሬ ችግኝ መትከል ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ለችግኞቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግም አረጋግጧል።
ሕፃን ፍሮምሳ ፍቅረማርያም በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በችግኝ ተከላ ላይ መሳተፉን ገልጾ፣ ችግኝ መትከል ንጹህ አየር ከማግኘት ባለፈ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልም ነው ብሏል።