ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን ለአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይኖርብናል

ጋጮ ባባ ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን ለአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን ገለጹ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በመገኘት ዞናዊ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስጀምረዋል።


 

ዋና ዳይሬክተሯ መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን ለአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይኖርብናል። 

''የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዘመቻው ተስፋን ለልጆቻችን በመትከል ታሪካዊ ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ልዩ ቀን ነው''  ብለዋል፡፡ 

ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን እስኪጸድቅ ድረስ ከንክኪ ነፃ በማድረግ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሐኪሜ አየለ፤ አረንጓዴ አሻራ ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስተላለፍ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። 


 

በዞኑ ጋጮ ባባ ወረዳ ባለፈው መጋቢት ወር በመሬት መንሸራተት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ የአንድ ጀምበር ዘመቻው ለዞኑ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል። 

በዞኑ በዛሬው ዕለት ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በችግኝ ለማልበስ የዞኑ ሕዝብ ከያለበት በነቂስ ወጥቶ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የጋጮ ባባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብሩክ ቡፃ፤ ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ፈጥረን ማስረከብ ይጠበቅብናል፣ ዛሬ ተባብረን ጋጮ ባባ ወረዳን ከተፈጥሮ ጋር ያስታረቅንበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌደራል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የጋሞ ዞንና የጋጮ ባባ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም