ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ የመበልጸግ ጉዞአችን አንዱ ሰበዝ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ የመበልጸግ ጉዞአችን አንዱ ሰበዝ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ የአንድ ሰሞን ዘመቻ ወይም የአጭር ጊዜ ግብን ታሳቢ ያደረገ ቁንጽል እርምጃ ሳይሆን፣ እንደ ሀገር የመበልጸግና የሁለንተናዊ እድገት ጉዞ አካል ነው ብለዋል።

ሥልጣኔ የነጠላ ተግባር ውጤት ባለመሆኑና የአንድ ዘርፍ እድገትም ብቻውን ስለማያሰለጥን፣ አረንጓዴ ዐሻራ የትልቁ ሀገራዊ ዓላማ አንድ ሰበዝ እና ሌላኛው የሥልጣኔ መሰረት እንደሆነ አመልክተዋል።


 

ሥልጣኔ ባዶ አየር ላይ እንደማይገነባና ጠንካራ መሰረት እንደሚፈልግ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሰረት ሳይጸና የሚገነባ ነገር በቀላሉ ፈራሽ እንደሆነና እንደማይዘልቅ ተናግረዋል።

ዘመናትን የሚሻገር ሥልጣኔ በመሰረቱ ጥልቀት እንደሚታወቅ በመግለጽ፣ የዛሬው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ልክ እንደ ኢነርጂ ልማት፣ የኢንደስትሪ ማስፋፋት እና የክህሎት ግንባታ ከብዙ የሥልጣኔ መሰረቶች አንዱ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

በተጨማሪም ለጠንካራ ሥልጣኔ የስነ-ምኅዳራዊ ዘላቂነትን አስፈላጊነት አስምረውበታል።




ሀገረ-መንግሥታዊ ግንባታን ለማጠናከር ተቋማት እንደሚገነቡ፣ አብሮነትን ለማጠናከር ሀገራዊ እርቅና ምክክር ላይ እንደሚሰራ፣ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ኢንዱስትሪና ዲጂታል ዘርፎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ እንዲሁም አስተዳደራዊ ልህቀት ላይ እንደሚሰራ ሁሉ፤ ስነ-ምኅዳራዊ ዘላቂነትን ለማምጣት በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አብሮነት ካልተጠበቀ፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ካልተካሄደ እና ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ካልጠነከረ ሥልጣኔ እንደማይሳካና እንደማይዘልቅ ሁሉ፤ ስነ-ምኅዳራዊ ዘላቂነት ካልመጣ ሥልጣኔ ሊዘልቅ እንደማይችልና የአንዱ መጉደል ሥልጣኔን ምሉዕ እንደማያደርገው ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተስፋን በመትከል መሰረታችንን እናጽና ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም