የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ የምናስረክብበት ትልቅ ተስፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ የምናስረክብበት ትልቅ ተስፋ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 27/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ የምናስረክብበት ታላቅ ተስፋ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ግብ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለምለሚቷን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ የምናስረክብበት ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።
ዛሬ ለምለም ኢትዮጵያን ለመገንባት በእጆቻችን ዝቅ ብለን የምንትክልበት፣ በሐሳብ አንድ ሆነን በተግባር ሀገራችንን በአረንጓዴ የምናልብስበት መርሃ ግብር ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር እየተከልን ያለነው ምግባችንን፣ ጥላችንን እና ውበታችንን ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ ተግዳሮቶችን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በሀገራችን ባለፉት ሰባት ዓመታት 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፤ ይህም በጋራ እና በትብብር የሰራነው የዘመናችን ታላቅ ውርስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን በተዘጋጁ ቦታዎች ላይ ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የተተከሉትን ችግኞች በአግባቡ መንከባከብና መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡