የተከልናቸውን ችግኞች ተንከባክበን ለታለመላቸው ዓላማ እናደርሳለን - የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተከልናቸውን ችግኞች ተንከባክበን ለታለመላቸው ዓላማ እናደርሳለን - የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች
ጊምቢ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ዛሬ የተከሉትን ችግኞች ተንከባክበው ለታለመላቸው ዓላማ እንደሚያደርሱ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ተሳታፊ የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው የ"አንድ ጀምበር" የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፣ የዞኑ ማኅበረሰብ ከማለዳ ጀምሮ በነቂስ በመውጣት አሻራውን እያኖረ ይገኛል።
ነዋሪዎቹ በዛሬው ዕለት በ"አንድ ጀምበር" የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው ለታለመላቸው ዓላማ እንደሚያደርሱ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ እየተሳተፉ ካሉት ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መሠረት ጎቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብ ዋስትና፣ አየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም፣ ለመድኃኒትነት፣ ለአፈር ለምነት እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት የሚያኖር በመሆኑ አሻራቸውን በማኖር ላይ ናቸው።
"ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይደለም" ያሉት ወይዘሮ መሠረት፣ የተተከሉትን ችግኞች ተንከባክበው ለቁምነገር እንደሚያበቁና የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሠሩ የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ነዋሪ አቶ አለማየሁ አዱኛ ናቸው።
አቶ አለማየሁ አክለውም፣ "ዛሬ በጋራ በመሆን በ''አንድ ጀምበር'' የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ያሳየነውን ተሳትፎና ተግባር፤ ችግኞቹን በመኮትኮትና ከእንስሳት ንክኪ መጠበቅ አለብን" ብለዋል።
"ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች ትውልድን ያገናዘቡ አሻራዎች በመሆናቸው በደስታ እየተሳተፍን ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኤቢሴ ታዬ ናቸው።
የሚተከሉት ችግኞች ከምግብነት በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ በመሆናቸው፣ ተክለው እንደ ህፃናት ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የላሎ አሳቢ ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዱኛ እንደተናገሩት፤ በዛሬው ዕለት በወረዳቸው በ"አንድ ጀምበር" የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው።