የምንተክለው ተስፋን ፣ለነገ ትውልድ የምናስተላልፈው ደግሞ ለምለሟ ኢትዮጵያን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምንተክለው ተስፋን ፣ለነገ ትውልድ የምናስተላልፈው ደግሞ ለምለሟ ኢትዮጵያን ነው
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የምንተክለው ተስፋንና የኢትዮጵያ ብልፅግናን፣ ለነገ ትውልድ የምናስተላልፈው ደግሞ ለምለሟ ኢትዮጵያን ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸዉ እንኳን ለ8ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ቀን አደረሰን ! በማለት ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል አገራዊ ንቅናቄ በአዲስ አበባችንም በሰፊ ንቅናቄ እየተተከለ ነው ብለዋል፡፡
ለአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብሩ 176 የሚሆኑ ቦታዎች ተለይተዋል፤ የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን በሚጨምር መልኩ በባለሙያ እየታገዘ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የምንተክለው ተስፋን ፤ የኢትዮጵያ ብልፅግና፥ ለነገ ትውልድ የምናስተላልፈው ለምለሟ ኢትዮጵያን በምናባችን አይተን፥ በሃሳብ አንድ ሆነን፥ በተግባራችን በእጆቻችን ተክለን ውዷን ሃገራችን አረንጓዴ እያለበስናት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የምንተክለው ምግባችን፥ ጥላ፥ ውበት ነው፤ እየተከልን ያለነው ነገ በአየር መዘባት ምክንያት የሚወጣውን የብክለት፥ የጤና ችግር፥ የጎርፍ አደጋን አስቀድመን ለመከላከል ነውም ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ህጻናት፥ ወጣቶች፥ ሴቶች አዋቂዎች ፥ አዛውንቶች በጋራ የምናሳካው ነው ያሉት ከንቲባዋ የተከልነውን በጋራ እንንከባከብ፥ እንጠብቅ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡