ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም እያከናወነችው ያለው ተግባር ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም እያከናወነችው ያለው ተግባር ውጤታማ ነው
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም እያከናወነችው ያለው ተግባር ውጤታማ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ተናገሩ።
በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ኩይዋታ ተፋሰስ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም እያከናወነችው ያለው ተግባር ውጤታማ ነው።
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በዛሬው ዕለት በመላ ሀገሪቱ የሚካሔደው የ800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ታሪካዊ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ችግኝ የመትከልና መንከባከብ ባህል እየጎለበተ የመጣ ሲሆን፣ የደን ሽፋኑም እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ባለው የተከላ መርሐ ግብር የአካባቢው ማኅበረሰብ ከጠዋቱ ጀምሮ አሻራውን በማሳረፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፤ ተባብረንም የሀገራችንን የብልጽግና ግብ ለማሳካት ጥረታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስጦታው ካምባታ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
መትከል ብቻ ሳይሆን ለእንክብካቤ በተሰጠው ትኩረት የፅድቀት መጠኑም እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በርካታ የከተማው ማኅበረሰብና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የክልሎች አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነሮች፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።