ቀጥታ፡

ዛፍ ተስፋ ነው፤እየተከልን ያለነው ነገን እና የልጆቻችንን መጻኢ ዕድል ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ዛፍ ተስፋ ነው፤ እየተከልን ያለነው ነገን እና የልጆቻችንን መጻኢ ዕድል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማለዳው ጀምሮ በነቃ ተሳትፎ በመረባረብ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤ አይ) ዩኒቨርሲቲ በመገኘት የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለማቋረጥ ክረምቱን በሙሉ ዛፍ በመትከል ኢትዮጵያን የማልበስ እና ዘላቂ ለውጥ የማምጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የዚህ ሀገራዊ ጥረት ዋነኛ ዓላማም ኢትዮጵያ እንድትበለፅግ፣ እንድትበራ፣ እንድትለወጥ፣ እንድታድግ እና እንድትሰለጥን ያለውን ትልቅ ሕልምና መሻት እውን ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

እንዲህ ዓይነቱ ትልቅ ሀገራዊ ሕልም ሊሳካ የሚችለው አስተማማኝ መሠረት ሲጣል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስነ-ምህዳር በኩል መሠረት መጣል ማለት አፈርን፣ ውሃን እና ተራራን መጠበቅ እንደሆነ አብራርተዋል።

እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ሥራ ለነገው ትውልድና ለልጆች የሚደረግ ኢንቨስትመንት መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "እየተከልን ያለነው ተስፋን፣ ነገን እና ኢትዮጵያን ነው" ብለዋል።

ይህም በትብብር እና በጋራ ጥረት የሚከናወን እንደሆነም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለው ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና ማግኘቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን አርአያነት እና አካሄድ ለመከተል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት የዓለም መንግሥታት የኢትዮጵያን ጥረት እውቅና በመስጠት፣የሽልማት አሰጣጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 32) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መወሰናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኮፕ ጉባኤ በዓለም ደረጃ አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎች እና ቢያንስ እስከ 100 የሚደርሱ የሀገራት መሪዎች የሚታደሙበት ትልቁ ስብሰባ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህንን መሰል ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ኢትዮጵያም ሆነች ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አዘጋጅተው እንደማያውቁ አስታውሰዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ ያማረች፣ የለበሰች፣ እያደገች ያለች እና ተስፋ ያላትን ገጽታዋን ለዓለም የምታሳይበት፣የተጨባጭ ልምዷን የምታካፍልበት እንዲሁም በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞችን የምታገኝበት ትልቅ መድረክ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኮፕ ጉባኤን ለማዘጋጀት በምታደርገው ዝግጅት ዓመቱን ሙሉ ግንባታ፣ ተከላ እና የጽዳት ሥራዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅሰው፣ የተባበረ ሕዝብ ሀገር መገንባት እንደሚችል ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ዛፍ የምግብ፣ የጥላ፣ የውበት እንዲሁም የመሬት መሸርሸርን የሚከላከል ዘብ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን በጀመሩት መንገድ በመተባበር የያዙትን ሀገራዊ ግብ እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም