ቀጥታ፡

መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦  መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።  

በአረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሰባት ዓመታት በክረምቱ ሳናቋርጥ ኢትዮጵያን ለማልበስ እና ለኢትዮጵያ መሰረት ለመጣል መላው ኢትዮጵያውያን ጥረት ሲያደርግ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን ጥረት ሀገራቸው እንድትለማ፣ እንድታድግ፣ እንድትለወጥና ያላቸው ጽኑ ፍላጎት መገለጫ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያን ህልሞች ለማሳካት አስተማማኝ መሰረት መጣል እንደሚገባ ጠቅሰው መሰረት ከሚጥሉ ስራዎች አንዱ የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ መሆኑን አመልክተዋል። 
  
አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ የአንድነት እና ትብብር ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህ የአረንጓዴ ልማት ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቶ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ)ን ለማስተናገድ መመረጧን ተናግረዋል።

የኮፕ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እያከናወነች ያለው ስራ እውቅና ያገኘበት ነው ብለዋል። 


 

አሁን እየሰራን ያለነው ለልጆቻችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የሚተከለው ችግኝ የነገውን ትውልድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ተስፋን እንትከል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው የ800 ሚሊዮን ችግኝ ግብ እና በአጠቃላይ ለዘንድሮ ዓመት የተያዘው የአረንጓዴ ዐሻራ እቅድ እንዲሳካ ኢትዮጵያውያን እንዲረባበረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

#ኢዜአ#አረንጓዴዐሻራ#ተስፋንእንትከል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም