የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን ወደ አሜሪካ አመራ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን ወደ አሜሪካ አመራ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት፣ ዩጂን ከተማ በሚካሄደው 21ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን ምሽቱን ወደ ውድድሩ ስፍራ አቅንቷል።
ሻምፒዮናው በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ታሪካዊ መድረክ በሆነው በሄይዋርድ ፊልድ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን፣ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ወጣት አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ሻምፒዮናው ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
በዘንድሮው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ5000 ሜትር፣ 3000 ሜትር፣ 1500 ሜትር፣ 800 ሜትር (በሁለቱም ፆታዎች)፣ 3000 ሜትር መሰናክል (በሴቶች)፣ 400 ሜትር (በሴቶች) እንዲሁም በርምጃ ውድድር (በሁለቱም ፆታዎች) ትሳተፋለች።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በሻምፒዮናው ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅታቸውን አድርገዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) እና የፌዴሬሽኑ የስልጠና፣ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አሰፋ በቀለ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት ልዑክ ቡድኑን መሸኘታቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
በዘንድሮው ሻምፒዮና ላይ ከ147 ሀገራት የተውጣጡ ከ1800 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
እ.አ.አ በ2024 በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 6 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ በመሆን ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።