ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በማጽናትና የጸረ ሰላም ኃይሎችን ከንቱ ዓላማ በማምከን የሚያኮራ ተግባር እየፈጸመ ነው - ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በማጽናትና የጸረ ሰላም ኃይሎችን ከንቱ ዓላማ በማምከን የሚያኮራ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ የሥራ ክፍሎች፣ አመራሮች፣ አባላትና ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ የፖሊስ አመራሮች፣ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በዚሁ ወቅት፤ አዲስ አበባ በተከናወኑ ልማቶች ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአፍሪካ ተጠቃሽ ከተማ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።

ይህ እውን እንዲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ የጎላ ሚና መጫወቱንም አድንቀዋል።

መንግሥት ዜጎችን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን ጥረቶች ለማሰናከል የሚንቀሳቀሱ የጸረ ሰላም ኃይሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በተቀናጀ የአሰራር ሥርዓት የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በማጽናትና የጸረ ሰላም ኃይሎችን ከንቱ ዓላማ በማምከን ያስመዘገበው ውጤት የሚያኮራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም መላው የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራርና አባላት የጸረ ሰላም ኃይሎችን ተልዕኮ በማክሸፍ የተገኘውን ስኬት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል እና ወንጀል ሲፈጸም ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ በመስጠት ረገድ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም