ከህብረተሰቡ እና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
ከህብረተሰቡ እና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት ከህብረተሰቡ እና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን አስታወቀ።
ዋና ጠቅላይ መምሪያው በ2018 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የስራ ክፍሎች አመራርና እና አባላት እንዲሁም ተቋሙ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው መርሀ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ የፖሊስ አመራር እና አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠቅላይ መምሪያው ከህዝቡ እና ሌሎች ፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።
ዓመቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ ትላልቅ አህጉራዊ ኹነቶች የተካሄዱበት መሆኑን አስታውሰው፤ ኹነቶቹ በስኬት እንዲካሄዱ የከተማው ፖሊስ ከተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን አመርቂ ስራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገለግሎት ህዝቡን ተሳታፊ በማድረግ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በዚህም የመዲናዋን ሰላም በማጽናት ረገድም ተጠቃሽ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
ዋና ጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ አባላቱን ውጤታማነት ይበልጥ የሚያልቁ አሰራሮችን እየተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለፖሊስ አባላት መኖሪያ የሚሆን ባለ 15 ወለል ህንጻዎች ግንባታ መጀመሩን አስታውሰው፤ የዋና መምሪያው ቢሮ ዕድሳትም በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል።
የዛሬው የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር በቀጣይም የሚከወኑ ስራዎች በላቀ ተነሳሽነት እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።