ችግኞች ተለይተው ለተከላ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ችግኞች ተለይተው ለተከላ ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፦ ነገ በሚካሄደው የአንድ ቀን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞች ተለይተው ለተከላ ተዘጋጅተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በአንድ ክንድ ተባብረው፣ በአንድ ቀን 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ አዲስ ታሪክ እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት ባደረገው ቅኝት በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የችግኝ ጣቢያዎች ለነገው የአንድ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚያስፈልጉ ችግኞችን የማዘጋጀት፣ የመለየትና የማጓጓዝ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ተመልክቷል።
በየጣቢያዎቹ ለአካባቢው አየር ንብረትና አፈር ተስማሚ የሆኑ የጥላ፣ የፍራፍሬና የሀገር በቀል ችግኞች ተለይተው ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል።
የተዘጋጁት ችግኞች ሳይበላሹና ሳይጎዱ ወደሚተከሉበት ቦታ በፍጥነት እንዲደርሱ ለማድረግም የተቀናጀ የትራንስፖርት አቅርቦትና የማከፋፈል ሥርዓት ተዘርግቶ ሥራዎች ተጠናቀዋል።
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ተነሳሽነት ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።