የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ትንሳኤ ብስራት!! - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ትንሳኤ ብስራት!!
በሐዊ አጫሉ
መግቢያ፡- የኢንዱስትሪ ዘርፍ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬን ከሚወስኑ ዋነኛ የብልፅግና ማረጋገጫ ምሰሶዎች መካከል በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ዘርፉ ምርትን ከማሳደግ ባሻገር የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የሀገር ውስጥ ምርታማነትን የሚያፋጥን የልማት ሞተር ነው። ኢትዮጵያም ከግብርና መሠረት የተነሳ ኢኮኖሚዋን ወደ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ሁሉን አቀፍ የምርት ሥርዓት ለማሸጋገር ከምታደርገው ጥረት መካከል ኢንዱስትሪውን በቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶነት በማካተት እየሰራችበት ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና ቴክኖሎጂ አምስት ዐበይት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ምሰሶዎች ተመሥርቶ እየተመራ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ኢንዱስትሪው የምርት አቅምን በማሳደግ የግብርና ምርቶችን ወደ ተጨማሪ እሴት በመቀየርና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እያስገኘ ነው። ይህንን ሽግግር እውን ለማድረግ የምርት አቅምን ማሳደግ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ማሻሻል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን እና የሰው ኃይል ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ የቀድሞ ገጽታ፤ ከመዋቅራዊ ተግዳሮት ወደ ለውጥ መንገድ!!
በቀደሙት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለያዩ ዕድሎችንና ፈተናዎችን በማስተናገድ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ሀገሪቱን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር በተደረጉ ጥረቶች የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል።
እነዚህ ፓርኮችም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተሞከረበት ወሳኝ ምዕራፍ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይህ ጉዞ በበቂ መሠረተ ልማት፣ በተሟላ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና በተቀናጀ የምርት ሰንሰለት እጥረት ምክንያት በበርካታ ፈተናዎች ለመውደቅ ተገዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ውስንነት፣ ዕውቅትና ክህሎትን የተሰላበሰ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የፋይናንስ እጥረት፣ ውስብስብና አስቸጋሪ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትና የገበያ ትስስር እጥረት የዘርፉን እድገት ገድበው የነበሩ ሁነኛ ተግዳሮቶች ናቸው።
ከመዋቅራዊ ተግዳሮት ወደ ምርታማነት፤ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ የለውጥ ፍኖት!!
ባለፉት ዓመታት በኢንዱስትሪ ዘርፉ የተስተዋሉ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታትና የሀገሪቱን የማምረት አቅም ለማሳደግ አዳዲስ የለውጥ አቅጣጫዎች ተነድፈው ተተግበረዋል። በተለይም ኢንዱስትሪን ከተለመደው የምርት ሥርዓት በማሻገር ወደ ተወዳዳሪ ዘመናዊና ውጤታማ የማምረቻ ማዕከል ለመቀየር የተለያዩ የፖሊሲማሻሻያዎች ተደርገዋል።
የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ማስፋት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን፣ የሰው ኃይል አቅምን ማሳደግና የግብርና-ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር በዘርፉ የተወሰዱ ሁነኛ የለውጥ እርምጃዎች ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያን አምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት በማጎልበት ከሀገር ውስጥ ገበያ እስከ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ድረስ ውጤት እያስገኘ ነው።
የግል ባለሃብቱ ሚና፤ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሞተር!!
የኢንዱስትሪ ልማት በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም። የግል ዘርፉ በካፒታል፣ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂና በአስተዳደር ብቃት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ለዘርፉ ዕድገት የማይተካ ሚና አለው። በዚህ ረገድ የግል ባለሃብቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋና አጋር እንዲሆን የሚያስችሉ ማዕቀፎች ተሻሽለው እየተሰራባቸው ይገኛል። ይህም የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት በማሻሻል፣ የንግድ ሥራ ሂደቶችን በማቀላጠፍ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋትና የምርት አቅምን በማሳደግ የግሉን ዘርፉ የምርታማነት አቅም እያጎለበተ ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ የአምራች ኢንዱስትሪ የትንሳኤ ብስራት!!
በሀገራችን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ውስጥ የምርትና አገልግሎት አሰጣጥን በማቀናጀት አዲስ ምዕራፍ ከከፈቱ ዐበይት ሀገራዊ መርሃ-ግብሮች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። ይህም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት ባህልን በማሳደግ ዘርፉ ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ሁነኛ ዕድልን ፈጥሯል። ንቅናቄው የማምረት አቅምን በማሳደግ ሥራ ያቆሙ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ መመለስ፣ የአምራቾችን ችግሮች በፍጥነት መፍታትና አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ዘርፉ በመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል።
በዚህ ሂደት በፋይናንስ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በውጭ ምንዛሬና በተቋማዊ ቅንጅት ረገድ የተወሰዱ እርምጃዎች የአምራች ዘርፉን የምርታማነት አቅም በማጎልበት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያንሰራራ በማድረግ የምርታማነት አብዮት እንዲቀጣጠል እያደረገ ይገኛል። የንቅናቄው ዋና ዓላማ በአምራች ዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት የኢትዮጵያን የማምረት አቅም ማሳደግ ነው። ይህም ሥራ ያቆሙ ወይም በአቅማቸው ልክ ያልሠሩ ፋብሪካዎችን ወደ ሙሉ ምርት በመመለስ የአምራቾችን ችግር በተቀናጀ መንገድ መፍታት፣ የፋይናንስና የግብዓት ተደራሽነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጓል።
በዚህ ሂደት የማምረቻ ዘርፉ በአዲስ የሥራ ባህል፣ በተቋማዊ ቅንጅትና በፈጣን ውሳኔ አሰጣጥ እየተመራ መሆኑ የለውጡን ፍጥነት እያሳደገው ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ተደራሽነትን ማሻሻልና የምርት ጥራትን ማረጋገጥ የኢንዱስትሪው ትንሳኤ ዋና ማሳያዎች ናቸው።
ለአብነትም፡-
የፋይናንስ አቅምና የብድር አቅርቦት ማሻሻል፡- የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዋነኛ እንቅፋት የሆነውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ በተደረገው ርብርብ፣ የብድር አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት 40 ቢሊዮን ብር ወደ 115 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል በማድረግ ለአምራቾች ሰፊ የካፒታል አቅም መፍጠር ተችሏል።
የውጭ ምንዛሬ ግኝትና የግብዓት ድጋፍ ማደግ፡- ንቅናቄው ከመጀመሩ በፊት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ይቀርብ የነበረው የውጭ ምንዛሬ መጠን አሁን ላይ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲደርስ ተደርጓል። ይህም ፋብሪካዎች ከአቅማቸው በታች እንዲሠሩ ያስገድድ የነበረውን የምርት ውስንነት በከፍተኛ ደረጃ አቃሎታል።
የምርት ዕድገት፣ ተኪ ምርትና የኤክስፖርት አፈጻጸም፡- ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከነበረበት 348 ሚሊዮን ዶላር ወደ 5.9 ቢሊዮን ዶላር በማደግ ግዙፍ ሀገራዊ ድል ተመዝግቧል። እንዲሁም በኤክስፖርት ገበያ የሚገኘው ገቢ ከ385 ሚሊዮን ዶላር ወደ 607 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለት ችሏል።
ተቋማዊ ቅንጅትና አዲስ የሥራ ባህል ማዳበር፡- በክልሎችና በፌዴራል ተቋማት መካከል የነበረውን የቢሮክራሲ ጫና በመቀነስ ፈጣን ውሳኔዎች እንዲሰጡ መደረጉ፤ እንዲሁም ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርትን በኩራት የመጠቀም እና የሀገር ፍቅር ስሜትን ከአምራችነት ጋር የማስተሳሰር ትልቅ ማህበራዊ ንቃተ-ህሊና መገንባት ተችሏል።
የወደፊት ተስፋ፤ ኢትዮጵያ አዲሲቷ አፍሪካዊት የኢንዱስትሪ ምርታማነት ተምሳሌት ሀገር!!
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጉዞ በቀጣይ ዓመታት ከተለመደው ማምረት ወደ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የምርት ሥርዓት እንዲሸጋገር ይጠበቃል። የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ አውቶሜሽን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና የፈጠራ ሥርዓቶችን ወደ ማምረቻ ዘርፉ ማስገባት የወደፊቱ ትኩረት ይሆናል።
በተመሳሳይም ጠንካራ የግብርናና ኢንዱስትሪ ትስስር፣ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የአህጉራዊ ገበያ ተደራሽነት የሀገሪቱ ቀጣይ የኢንዱስትሪ ግቦች ናቸው። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) የሚፈጥረውን ሰፊ የገበያ ዕድል በመጠቀም ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችል መሠረት እየጣለች ትገኛለች።
ማጠቃለያ፡- ማምረት፤ የኢትዮጵያ የብልፅግና ቁልፍ መሳሪያ!!
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጉዞ ከፈተና ወደ ዕድል፣ ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል፣ ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ተጨማሪ እሴት ያለው ምርት አቅራቢነት በማምራት እመርታዊ ውጤቶችን እያስገኘ ነው። የኢንዱስትሪውን አቅም ማሳደግ ማለት ፋብሪካዎችን ብቻ ማስፋፋት ሳይሆን የሀገርን ምርታማነት፣ የወጣቶችን ዕድል፣ የኢኮኖሚ ነፃነትንና የልማት ዘላቂነትን ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን የዛሬ ልማት ብቻ ሳይሆን የነገውን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚገነባ ሀገራዊ ራዕይ ነው።