ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን የሚገነባ ለአፍሪካም ተምሳሌት የሚሆን ታሪካዊ ሂደት ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥትና የጋራ መግባባትን የሚገነባ ለአፍሪካም ጭምር ተምሳሌት የሚሆን ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ፖለቲከኞች ገለጹ።

ዋናው የምክክር ጉባኤ በ4 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች መካከል ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

ፖለቲከኛው አበራ በቀለ ለኢዜአ እንዳሉት፤የምክክር ጉባኤው ለዘመናት ሲቆዩ በነበሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሠረታዊ ሀገራዊ አለመግባባቶች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተከፈተ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው የሕዝብ ውክልና የተሰጣቸው ተመካካሪዎችም ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረውን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የጋራ መግባባትን ለመፍጠር መድረኩን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅምና በምክክር መፍታት እንደሚችሉ የሚያሳይ በመሆኑ ለአፍሪካም ጠቃሚ ተሞክሮና ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ችግሮች በራሷ መንገድ በጋራ መግባባት መፍትሔ የምትሰጥ ሀገር ስትሆን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን የምታስጠብቅ ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና ፖለቲከኛ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ሰላምን፣ ብሔራዊ ደህንነትንና ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

አሁን እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት የይስሙላ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የቆዩ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮችን በተጨባጭ ለመፍታት የታለመ መሆኑን አስረድተዋል።

የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች አካታችና አሳታፊነትም ሁሉም ዜጋ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችና ችግሮች በማንጸባረቅ የጋራ ሀገራዊ መግባባትና አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ፖለቲከኞቹ እንደገለጹት፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን ችግሮች በዜጎቿ ምክክርና መግባባት ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል ከመሆኑም በላይ የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ በተግባር የሚያንጸባርቅ ሂደት መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅምና ችሎታ መፍታት እንደሚችሉ ጠንካራ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምክክሩ ውጤትም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውና ለመላው አፍሪካ በሰላም ግንባታ፣ በልማትና በጋራ መግባባት ረገድ ጠቃሚ ተሞክሮ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በውይይትና በሃሳብ የበላይነት የመፍታት የሰላም ባህልን በማጠናከር፣ ለቀጣዩ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆን ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም