ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ወርቃማ ዕድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ወርቃማ ዕድል ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የጋራ መግባባት ወርቃማ ዕድል መሆኑን ተመካካሪ ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መጀመሩ ይታወቃል።
በጉባኤው ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በመሳተፍ በአሁኑ ወቅት በዓበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነት እና የጋራ መግባባት መረጋገጥ እጅግ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት መድረክ ሆኗል።
ተመካካሪ ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል፣ በምክክር ሂደቱ በከፍተኛ ደስታና አክብሮት እየተሳተፉበት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አራት ሺህ ተመካካሪዎች ለሀገሪቱ ሰላም እና የጋራ መግባባት የሀሳብ ፊት አውራሪ ሆነው እንደሚወጡ ትልቅ እምነት እንዳላቸው አንስተዋል።
በመድረኩ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በግልጽ በማንጸባረቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ከዚህ አሳታፊ ሂደት ትልቅ ትምህርት እና ልምድ መቅሰም እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
መድረኩ የመሸናነፍ ሳይሆን ሀገራዊ መግባባት የሚገነባበት ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን ታሪካዊ የምክክር ሂደት ተስፋ የጣሉበት መሆኑን አንስተዋል።
ሰላማዊ የመፍትሔ ማዕድ በሆነው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሰባስቦ መመካከር የተሻለ እና የሰለጠነ አካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የየትኛውም አካባቢ ችግር የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በጋራ መግባባት እና በአብሮነት መንፈስ የጋራ መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት በተለይም ልሂቃን በዘመናቸው ያካበቱትን ልምድ፣ ያነበቡትን እና ያወቁትን ወደ መሬት አውርደው ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸውን አዎንታዊ ሚና የሚያበረክቱበት ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል።
በመሆኑም ያላቸውን ሀሳብ ሰብሰብ አድርገው ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት አስተማማኝ መሠረት እንዲጥሉ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።