አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮችን እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮችን እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2018(ኢዜአ)፦አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮችን እያጎለበተ መሆኑን ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ሰኔ 8 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ አስጀምረዋል።
በወቅቱም የዘንድሮው መሪ ሃሳብ የነገን ብሩህ ተስፋ ዛሬ በመትከል የወደፊቱን ብልፅግና መሠረት የሚጥል፤ የተተከሉ ችግኞች ሥር የብልፅግና ግንድ፣ ቅርንጫፍና ፍሬ በመሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ሃብት እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም "ተስፋን እንትከል" በመሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል የተገኘውን ታሪካዊ አርአያነት በአረንጓዴ ዐሻራ በመድገም የኩራት ምንጭ የሆነች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚሁ መሠረትም መላው ኢትዮጵያውያን ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ የልማት ታሪክ እንዲጽፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞች በብዙ መንገዶች የኢትዮጵያውያንን ሕይወት እየቀየሩ ናቸው።
መርሃ ግብሩ የፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድልም የአትክልትና ፍራፍሬ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ለወጪ ንግድ ዕድገት ጭምር አወንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ የዝናብ ውሃ የመሬት መሸርሸር አደጋን በመቀነስና በመከላከል፣ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይህም የመሬት ውስጥ የውሃ ክምችትን በማሳደግ የተፈጥሮ ምንጮች፣ ጉድጓዶችና ወንዞች የውኃ መጠን እንዲጨምር እያገዘ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የተፋሰስ ሥነ-ምህዳርን በማጠናከር የደረቁ ምንጮች እንደገና እንዲያገግሙ ማስቻሉን ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ በውሃ አካላት ላይ ከፍተኛ የመጠንና የውሃ ሃብት አቅም ውጤት ማምጣቱንም በዓባይ፣ አዋሽና ሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች ተፋሰስ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ደርቀውና ጠፍተው የነበሩ የውሃ ምንጮችን በመመለስና በዝናብ ወቅት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
የሐሮማያ ሐይቅ መመለስም በኢትዮጵያ የሥነ-ምህዳር ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡ ትልልቅ ስኬቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የውሃ ሃብትን፣ የተፈጥሮ ሥርዓትንና ዘላቂ ልማትን በማጠናከር ወደ ወንዞች ይገባ የነበረውን ደለል በመቀነስና የግድቦችን ደኅንነት በመጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮች እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።