ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ አዲስ የምክክር ልምምድን የከፈተ ታሪካዊ ዕድል ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለኢትዮጵያ አዲስ የምክክር ልምምድን የከፈተ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። 

የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጉባኤው የግልና የቡድን ፍላጎቶችን በማጥበብ ሀገራዊ ጥቅምን በማስቀደም፣ በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ነፃና አሳታፊ ምክክር እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለኢትዮጵያ አዲስ የምክክር ልምምድን የከፈተ ታሪካዊ ዕድል መሆኑንም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ ተመካካሪዎች ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ተወካይና ተመካካሪ ጣሂር መሐመድ እንዳሉት፤ በምክክር ጉባኤው ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ምክክር እየተደረገ ነው።

በዋናው የምክክር ጉባኤ የሚመከርባቸው ዐበይትና ንዑሳን አጀንዳዎችም በተመካካሪዎች መካከል በነፃነትና አካታችነት እየተመከረባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን መሠረታዊና መዋቅራዊ ችግሮች በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መግባባት በመፍጠር መፍትሔ የሚሰጥ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።


 

የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበርና ተመካካሪ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የመደማመጥና የመግባባት ባህልን በማጠናከር በተሻለ አሳታፊነት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከአጀንዳ ማሰባሰብና ከተሳታፊዎች ልየታ ሂደት ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን በተግባር በማረጋገጥ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል።

ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ሕዝብን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ ሃሳባቸውን በነፃነት በማንሸራሸርና በግልጽ ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ ምክክር እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገራዊ ችግሮችን በሰለጠነ ምክክር ለመፍታት፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ዘላቂ የሆነ መግባባት ለመፍጠር የተገኘ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባልና የጉባኤው ተመካካሪ ሙሐሙድ መሐመድ ሀሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች የኢትዮጵያን ብዝኅነት፣ ሕብረ-ብሔራዊ እሴቶችና የጋራ ሀገራዊ ጥቅሞችን በሚያንጸባርቁ ሃሳቦች ላይ እንዲመክሩ ዕድል ፈጥሯል።

ሀገራዊ አለመግባባቶችን በጦር መሣሪያ በታገዘ ግጭትና በኃይል ለመፍታት መሞከር ዘላቂ መፍትሔ የማያማጣና አዋጭ ያልሆነ አካሄድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም የጋራ ሀገርን በመገንባት አዲስ የምክክር ታሪክ እየጻፍን ነው ያሉት አቶ ሙሐሙድ፤ የጉባኤው አጀንዳዎች ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የመግባባት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንትና ተመካካሪ ገነነ ገረቡ በበኩላቸው፤ በምክክር ጉባኤው አንዱ የሌላውን ሃሳብ መረዳት በሚያስችል መልኩ ማንኛውም የሕዝብ አጀንዳ በነፃነት እየተንጸባረቀ ነው ብለዋል።

የምክክር ጉባኤውም ለዘመናት የቆዩ የአለመግባባቶችን ለቀጣዩ ትውልድ እንዳይተላለፉ ለማድረግ ስልጡን ምክክር እያደረግን ነው ብለዋል።

በተመካካሪዎች መካከልም በአርአያነት የሚወሰድ ነፃ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም