የአረንጓዴ ዐሻራ ሁለንተናዊ ምርታማነትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ ሁለንተናዊ ምርታማነትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2018(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሁለንተናዊ ምርታማነትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ገጽታ እያጎለበተ ያለ ውጤታማ ሀገራዊ የልማት ተነሳሽነት መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ከመትከል የተሻገረ የኢትዮጵያ የአካባቢ ደኅንነት፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የሥነ-ምኅዳር ሚዛንና ዘላቂ ልማት የሚያጎለብት ሀገራዊ የልማት ግብ ሆኖ ቀጥሏል።
በየዓመቱ የሚካሄደው መርሃ ግብርም የዜጎችን በጎ ፈቃድ፣ የመንግሥት ቁርጠኝነትና የተቋማትን ትብብር በማቀናጀት ኢትዮጵያን ወደ እመርታዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞ አቅም እየሆነ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በሰኔ 8 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ አስጀምረዋል።
በወቅቱም የዘንድሮው መሪ ሃሳብ የነገን ብሩህ ተስፋ ዛሬ በመትከል የወደፊቱን ብልፅግና መሠረት የሚጥል፤ የተተከሉ ችግኞች ሥር የብልፅግና ግንድ፣ ቅርንጫፍና ፍሬ በመሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ሃብት እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የአካባቢና የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልፅግና የሚያጠናክር ብሔራዊ የልማት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን በማስታወስ፤ ዘንድሮም ከ8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ጠቅላላ ቁጥሩን 56 ቢሊዮን ለማድረስ ግብ መያዙን ገልጸዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም "ተስፋን እንትከል" በመሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል የተገኘውን ታሪካዊ ድል በአረንጓዴ ዐሻራ በመድገም የኩራት ምንጭ የሆነች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚሁ መሠረትም መላው ኢትዮጵያውያን ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ የልማት ታሪክ እንዲጽፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሲቪል ማኅበራት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአካባቢ ጥበቃና የሥነ-ምኅዳር ደኅንነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በስፋት ከሚሳተፉባቸው የልማት መስኮች መካከል ቀዳሚው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥነ-ምኅዳር ሥርዓት በመገንባት፣ የምርታማነት አቅምን በማሳደግና ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈ የልማት ተነሳሽነት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጤና እና አካባቢ ኮንሶርቲየም (PHE Ethiopia Consortium) ዳይሬክተር እንዳሻው ሞገሴ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በአካባቢ ጥበቃ፣ በሥነ-ምኅዳር ደኅንነት፣ በሥነ-ሕዝብና በጤና የልማት ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ የተመጣጠነ የሥነ-ምኅዳር ሥርዓትን በመገንባት፣ የብዝኃ ሕይወት ሃብቶችን በመጠበቅና የተጎዱ መሬቶችን በማገገም ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑንም አስረድተዋል።
መርሃ ግብሩ ሁለንተናዊ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያጠናክር፣ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድግና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታ የሚያጎለብት ዕውቅና እያስገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቀነስም የመሪነት ሚናን በመወጣት ተጨባጭ እርምጃ እየወሰደች የምትገኝ ቁርጠኛ ሀገር እያሰኛት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ የምርታማነት አቅም የፈጠረ ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት የደን ሽፋንን ለማስፋት፣ የብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሲቪል ማኅበራትም በየዓመቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቀጣይነት ያለውን ተሳትፎ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃና የዘላቂ ልማት ጥረቶችን እየደገፉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የዛሬን ትውልድ ከነገው ጋር የሚያስተሳስር፣ የአካባቢ ጥበቃን ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚያስተባብር፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልፅግና አሰናስሎ የሚያስቀጥል ሀገራዊ ተልዕኮ መሆኑን እየተረጋገጠ ነው።