የክልሎች ቅኝት - በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት - በወፍ በረር
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ) የክልሎች ቅኝት - በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል።
በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5 ዓመት 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በክልሉ የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን አንስተዋል።
የሜካናይዜሽን እርሻም ተግባራዊ በመደረጉ ከ55 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
ከማዕድን ዘርፍም በበጀት ዓመቱ ከ 8 ሺህ 900 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
ኦሮሚያ ክልል
በኦሮሚያ ክልል የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለበት በማድረግ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሪፎርም እየተተገበረ ይገኛል።
ለዚህም የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ትግበራ ይፋ የማድረጊያ መርሃ ግብር ''የአገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ለሁለንተናዊ ብልጽግና'' በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፤ የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችል እስከ ቀበሌ የደረሰ አሰራር መዘርጋቱን በወቅቱ አንስተዋል።
አልግሎቶችን በዲጂታል ስርዓት በመደገፍ የህዝቡን እንግልት፣ ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ይህም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሲዳማ ክልል
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ በክልሉ የ2019 የትምህርት ዘመን የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ማድረግና በግብአት ለማሟላት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ በማድረግ በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲታይ መደረጉንም አስረድተዋል።
ጋምቤላ ክልል
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2018 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማጃንግ ዞን በመንገሺ ወረዳ ያስጀመሩትም በዚሁ ሳምንት ነው።
በክልሉ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል ።
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ከማድረጋቸው ባለፈ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሯ ገልፀዋል።
አማራ ክልል
በአማራ ክልል የግብርናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች ግብአት ማምረት ተችሏል።
የዚሁ አካል የሆነው በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ 837 አርሶ አደሮች በማህበር በመደረጃት “የጅሩ-አግሮ ቢዝነስ“ ኩባንያን መስርተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ኩባንያው የአርሶ አደሮችን ምርት በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርብ ነው።
የአግሮ-ቢዝነስ ኩባንያውም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አርሶ አደሩ ከጥሬ ግብአት አቅራቢነት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስተርነት በማደግ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ በኮንታ ዞን አመያ ከተማ አስተዳዳር ዙሪያ ጨታ ቀበሌ የተገነባውን የባቾ ገጠር ሞዴል መንደር መርቀው ለነዋሪዎች አስረክበዋል።
በወቅቱም የሞዴል የገጠር መንደሩ መገንባት የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ውጤታማ በማድረግ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ብሎም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ በማጠናቀቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በተለይም የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የወረዳና ቀበሌዎች ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከርና የግብይት ሰንሰለትም እንዲቀላጠፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም በክልሉ ኮንታ ዞን በአመያ ዙሪያ ወረዳ በኡማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናት ችግር ያቃለለና ለመሰረተ ልማት ጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።
በመልእክታቸውም በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም በክልሉ በተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ 48 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግብር ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ለዚህም በህግና የአሠራር ስርአት በመታገዝ የገቢ አቅምን በማስፋት የክልሉን ዕድገት ዘላቂነት በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል ።
በ2019 በጀት አመትም የክልሉን የገቢ አቅም ለይቶ በተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ የግብር እቅድን ለማሳካት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት አመቱ 48 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ገቢውን ለማሳካትም የህግና የአሠራር ስርአት በመዘርጋት የክልሉ ዕድገት በዘላቂነት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
አፋር ክልል
በአፋር ክልል የእንሰሳትና ዓሳ ሀብትን በማልማት ለወጣቶች የስራ እድልን ለማስፋት የተሰሩ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ የእንሰሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ገልጸዋል።
ለዚህም ስምንት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሐይቆች ላይ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ አሳ ልማት ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
ለአብነትም በአፋምቦ ሐይቅ ላይ 200 ወጣቶች በዓሳ ሀብት ልማት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋቱን አስረድተዋል።
በዓሳ ሀብት ልማቱ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች እንዳሉት የአሳ ሀብትን አልምተው ተጠቃሚ ለመሆን በማህበር ተደራጅተው በመስራት ላይ ናቸው።
ስራውንም ለማሳካት ክልሉ እያደረገ ያለው የሙያ ስልጠናና ድጋፍ የማይተካ ድርሻ አለው ብለዋል።
ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "ሁሉ አቀፍ እመርታ ፣ ለሁለንተናዊ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግስት ስራ አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
ርዕስ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ በሰላም፣ በልማትና መልካም አስተዳደር የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎች ተከናውነዋል።
የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ክልሉን የህብረ ብሄራዊነት ተምሳሌት ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገኙ ስኬቶችን ማጠናከርና የተስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ የመድረኩ ዋና ዓላማ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ሐረሪ ክልል
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር እንደገለፀት፤ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ስራ በገጠር ወረዳዎች የመስኖ ልማት በስፋት ተከናውነዋል።
ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ የ2018 የግብርና ልማት እቅድ አፈጻጸምና የ2019 የግብርና ልማት መሪ እቅድ ላይ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የእንስሳት ተዋጽኦና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትልቅ እመርታ የተገኘበት ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባሻገር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ብለዋል።
ሶማሌ ክልል
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባዔውን ሲያካሂድ ርእሰ መስተዳድሩ ሙስጠፌ ሙሀመድ፤ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በክልሉ የሰላምና የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ስራዎችና የመጡ ውጤቶችን አብራርተዋል።
የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የፍትህ አካላትን አቅም ለመገንባት በተደረገ ጥረት የፍትህ ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን መቻሉንም አንስተዋል።
በክልሉ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በድህነት ቅንሳ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ የሚመጡ አደጋዎች ቅነሳም ከፍተኛ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።