በሶማሌ ክልል የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል
ጅግጅጋ፣ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ):- በሶማሌ ክልል የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የአከባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
የሶማሌ ክልል ሀገራዊውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ተግባራዊ በማድረግ በአካባቢ ጥበቃ፣ በደን ልማትና የብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ ስራዎች ላይ የተገበራቸው ተግባራት ለውጥ እያመጡ ነው።
ክልሉ ነገ ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር በችግኝ አይነቶች መረጣ፣ በቦታና የችግኝ ጣቢያዎች ዝግጅት እና ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ረገድ አስፈላጊዎቹን ዝግጅቶች ማጠናቀቁን ነው የገለጸው።
የክልሉ የአከባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ሙህዲን አብዲ
ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር አስፈላጊ ዝግጅት ተጠናቋል።
ሃላፊው በክልሉ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ የተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉም ተናግረዋል።
ካለፉት ቀናት ጀምረው ችግኞችን ከተለያዩ ጣቢያዎች ወደ ተከላ ቦታ የማጓጓዝ ሥራ ሲከናወን እንደነበር ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ በቂ ዝግጀት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም ከ1 ሺህ 140 ሄክታር በላይ መሬት በደን ለመሸፈን መታቀዱን አንስተው፤ 91 የችግኝ ተከላ ቦታዎች ተለይተው አስፈላጊውን የጉድጓድ ቁፋሮና የችግኝ ማጓጓዝ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞች አድገው ለተፈለገው ጠቀሜታ እንዲበቁም የመከታተልና የመንከባከብ ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ኢንጂነር ሙህየዲን በነገው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነውን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐግብር ህብረተሰቡ በስፋት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።