ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።


 

በቆይታቸውም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተካሄደ ሕዝቡም ያለ አንዳች መሰላቸት ረጅም ሰዓት ተሰልፎ ድምጹን የሰጠበት ነው ብለዋል፡፡

ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምርጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የሚገልጽበት መንገድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በምርጫ ሂደቱ መሳተፋቸው ብዙ ነገሮችን እንድንማር አድርጎናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላማችንን እንድንፈትሽ፣ ተቋሞቻችንን እንድንፈትሽና የሕዝቡን ስሜት ይበልጥ እንድንገናዘብ አድርጎናል ብለዋል፡፡

ከእንግዲህ በኋላ በኢትዮጵያ ከምርጫ ውጭ ሌላ የስልጣን ማግኛ መንገድ አለመኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስልጣንን በሰላማዊ መንገድና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ማግኘት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን አንስተው፤ ምርጫው ከፍተኛ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማንቂያም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዜጎች የተኩስ ድምፅ ሳያቆማቸው፣ ዝናብ፣ ብርድና ቁር ሳያቆማቸው ዋጋ ከፍለው ድምጻቸውን ለመስጠት የሄዱበት መንገድ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫው ኢትዮጵያውያን በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ አሉታዊ ሃሳቦችን ለመስማት ዝግጁ አለመሆናቸውን በተግባር ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሀገረ መንግሥት ግንባታና የመንግሥት መኖር ጥቅሙ ምን እንደሆነ ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም