በቤንች ሸኮ ዞን ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በቤንች ሸኮ ዞን ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝግጅት ተደርጓል
ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በቤንች ሸኮ ዞን ነገ ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ እንዳሉት ነገ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሔደው ሀገር አቀፍ የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በዞኑ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉም ነው የተናገሩት፡፡
በመርሃግብሩ የዞኑን የፍራፍሬ ልማት ተስማሚነትና ምርታማነት አቅምን ወደ ላቀ ውጤት ለማሸጋገር እየተሠራ ያለውን ሥራ በሚያጠናክር መልኩ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።
የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከልና የውሃ ምንጮችን ከአካባቢ አየር ንብረት ሚዛን ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር የማቆየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ደን መጠበቅና የሳሳው ላይ ችግኝ ተክሎ በመተካት ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ተግባርም የዚሁ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካል ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ነገ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በዞኑ በቂ የችግኝ አቅርቦት እና የጉድጓድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ሌሎችም የፍራፍሬ አይነቶች በዞኑ በስፋት ከሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ካላቸው ችግኞች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።