በአዳማ ከተማ አስተዳደር ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ አስተዳደር ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተደርጓል
አዳማ፤ ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ አስተዳደር ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመከላከል፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ እና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር "የአረንጓዴ አሻራ" ኢኒሼቲቭ በየዓመቱ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል።
ከዚህ ሀገራዊ ዘመቻ ዋና ዋና ስልቶች መካከል ህብረተሰቡን በአንድ ጀምበር በማንቀሳቀስ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መሬት ማሳረፍ አንዱ ነው።
ይህ "የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ" መርሃ ግብር የማህበረሰቡን አንድነት የሚያጠናክር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባህልን የሚያዳብር እና በአጭር ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዳ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
የአዳማ ከተማ አስተዳደርም ፈጣን የከተማ እድገት ከሚያሳዩ ከተሞች አንዷ በመሆኗ ለከተማዋ ውበትና ለምግብነት የሚሆኑ ተስማሚ የችግኝ አይነቶችን በማዘጋጀት እና የጉድጓድ ቆፋሮ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለነገው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ራሷን አዘጋጅታለች።
የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ እንዳስታወቁት ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ ችግኞችን የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ሐምሌ 27 ቀን 2018ዓ.ም በሚካሄደው በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
ለተከላ የተዘጋጁትን ችግኞች በሰው ሃይልና በተሽከርካሪ ወደሚተከሉበት ስፍራ የማጓጓዝ ስራዎች እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለከተማ ግብርናና ሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የከተማዋን ቆላማ አየር ንብረት ነፋሻማ ከማድረግ ባሻገር በሰብል ምርትና ምርታማነት እድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ መላው የከተማዋ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ሀገር በነገው እለት ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን ''የአንድ ጀምበር'' የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም መዋቅሮች አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም ከንቲባው አረጋግጠዋል።