ቀጥታ፡

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 26/2018 (ኢዜአ) ፡-በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት "የአረንጓዴ አሻራ" ኢኒሼቲቭን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል።

በዚህ ሀገራዊ ጥሪ መሰረት ባለፉት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በየዓመቱ ህዝቡን በአንድ ላይ በማንቀሳቀስ "በአንድ ጀምበር" በሚካሄድ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በርካታ መቶ ሚሊዮን ችግኞችን መሬት ማሳረፍ ተችሏል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርም የዚሁ ሀገራዊ ጥሪ አካል በመሆን በየዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን በስፋት ሲተገብር ቆይቷል። 

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ስጦታው ከምባታ ለኢዜአ እንደገለጹት በነገው እለት ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

በከተማው በተመረጡ አምስት የመትከያ ስፍራዎች ችግኞች ወደ ስፍራው የተጓጓዙ ሲሆን ለችግኝ ተከላው የሚሆን የጉድጓድ ቁፋሮና ሌሎች ለተከላው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ፈልተው ወደ መትከያ ስፍራው ከተላኩ ችግኞች ውስጥ የአቮካዶ፣ የፓፓያ፣ የዘይቱንና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች እንዲሁም ቡና፣ የውበትና የጥላ ዛፍ ችግኞች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 7 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉና በኮሪደር የለሙ አካባቢዎችም የውበትና የጥላ ዛፎች ችግኞች አንደተዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡

የእንስሳት መኖና ሌሎች ሀገር በቀል የአካባቢ ዝርያዎችም እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

ነገ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018ዓ.ም በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከከተማዋ 32 ቀበሌዎች የተውጣጡ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ተሳታፊ አንደሚሆኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም