የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በህልውናዋ የሚገዳደራትን ማንኛውንም ስጋት መመከት የሚያስችል አቅም አላት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በህልውናዋ የሚገዳደራትን ማንኛውንም ስጋት መመከት የሚያስችል አቅም አላት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በህልውናዋ የሚገዳደራትን ማንኛውንም ስጋት መመከት የሚያስችል አቅም እና ዝግጁነት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ጫካ የገቡ ኃይሎች በዋናነት “ለህዝብ ጥቅም እንቆማለን እና ለህልውናው እንታገላለን” ቢሆኑም በተግባር ግን እየታየ ያለው በተቃራኒው መሆኑን አንስተዋል።
እነዚሁ ሃይሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የጀመሩት ያልተቀደሰ ጋብቻ በየትኛውም መንገድ ከጥፋት በስተቀር ልማት ሊያመጣ እንደማይችል ተናግረዋል።
ከታሪካዊ ጠላቶች የማበር እና የኢትዮጵያን ጥቅም የማሳጣት ጉዳይ በታሪክ ውስጥ የነበረ መሆኑን አውስተዋል።
የውስጥ እንክርዳዶችና ሃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፍጠር ኢትዮጵያ የቀይ ባህር እንድታጣ በማድረግ የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በዚህም ምክንያት በርካታ ትውልዶችን ተጎጂ ያደረገ ታሪካዊ ጥፋት መፈጸሙንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እነዚህ ያልተቀደሱ ጋብቻዎች በኢትዮጵያ ላይ ጥቁር ጠበሳ ጥለው ማለፋቸውን ጠቅሰው ያለፈውን ታሪክ ለሚያውቅ ሰው አሁን ላይ ያለውን ነገር በግልጽ መረዳት ይችላለ ብለዋል።
አሁን ያለው ያልተቀደሰ ጋብቻ ሽርጉድ ከዚህ ቀደም ከነበሩ መሰል ጥፋቶች ውጪ ለኢትዮጵያውያን ጥቅም እንደማያመጣ አስገንዝበዋል።
የዛሬይቱ የኢትዮጵያ የያኔው ኢትዮጵያ አይደለችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ ከዛ ጊዜ መማሯንና የዛን ጊዜ ጥፋቶችና ስብራቶች አውቃ ተዘጋጅታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ባላት ህልውና የሚገዳደራት ከመንገዷ የሚያወጣት እንቅስቃሴ ትናንት በነበረው ደረጃ ስጋት እና ጥፋት እንደማያመጣባት ተናግረዋል።
እነዚህ ሃይሎች ከትናንትናው ጉዳይ ሊማሩ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያውያን የውስጥ ሃይሎች አዲስ ያልተቀደሰ ጋብቻ ለመፍጠር እያደረጉትን ያለውን እንቅስቃሴ በሰከነ መንገድ እንዲያስተውለውም አስገንዝበዋል።
የውስጥ ልዩነቶች፣ ችግሮች አለመግባባቶች ኢትዮጵያ ባላት የካበተ የእርቅና ሽምግልና ስርዓት መፍታት እንደሚቻል ገልጸው ከዛ ውጪ የውጭ ሃይሎችን ማስገባት ከጥፋት ውጪ የተለየ ነገር እንደማያመጣ ገልጸዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA