ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአማራ ክልል ሕዝብን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአማራ ክልል ሕዝብን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአማራ ክልል የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቆይታ በለውጡ ዓመታት በአማራ ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎችን አስመልከተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው እንደገለጹት፤ በለውጡ ማግስት ከአማራ ክልል ሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የፍትሐዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ በዋናነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። 

በወቅቱ የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በተካሄደው ጥናትም ክልሉ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበረ መረጋገጡንና ይህም በክልሉ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትን ማረጋገጥ ላይ ማነቆ እንደነበር አብራርተዋል።

ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው ለአብነትም ለ18 ዓመታት ግንባታው ሳይጠናቀቅ የቆየውን የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት በርካታ ሀብት በመመደብ ግንባታውን ወደ መገባደድ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም ለግድቦች ግንባታ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አክለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በለውጡ ማግስት 90 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የነበረው የክልሉ ዓመታዊ ምርት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች አሁን ላይ ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል። 

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ደግሞ ከለውጡ በኋላ የባሕር ዳር፣ የደብረ ብርሃን እና የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ነው ያብራሩት።

ከቱሪዝም አንጻርም የላሊበላ እና የአጼ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት እድሳቶች፣ የሎጎ ሐይቅ እና የፈለገ ግዮን ሪዞርት እንዲሁም የጎርጎራ ፕሮጀክት በቱሪዝም ዘርፍ የክልሉን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ዋና ዋና ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። 

የመሠረተ ልማት ግንባታን በተመለከተም የነበረው 2000 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን አሁን ወደ 4ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ማደጉን አንስተዋል። 

የባሕር ዳር እና የኮምቦልቻ የአየር መንገድ ተርሚናሎችን ጨምሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። 

በተጨማሪም በክልሉ የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ከነበረበት 20 በመቶ ወደ 40 በመቶ ሽፋን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው ይህ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ የበለጠ ይሰራል ነው ያሉት። 

በኮሪደር ልማት ፕሮጀክትም እንዲሁ በክልሉ በሚገኙ 32 ከተሞች በተሰራ የኮሪደር ልማት የከተሞቹ  ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲቀየር አስችሏል ነው ያሉት በማብራሪያቸው። 

በዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍም በ«አምስት ሚሊዮን ኮደርስ» ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን ማሰልጠን መቻሉንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት ልዩ ልዩ ፈተናዎችና እንቅፋቶች ቢኖሩም በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመጠጥ ውሃ ዘርፎች አመርቂ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። 

በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የሕዝቡ የመልማትና የመጠቀም ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም