ቀጥታ፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት የአማራ ክልልን ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የፕሪቶሪያው ስምምነት የአማራ ክልልን ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማስቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያ ስምምነትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቱ የጥይት ድምጽን በማስቆም ወደ ልማት ትኩረት እንዲደረግ ማስቻሉን ገልጸዋል። 

ስምምነቱ የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልልሎች አልፎም መላው ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል አብዛኞቹ የልማት ስራዎች የተከናወኑት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ መሆኑ ክልሉን ተጠቃሚ ያደረገ እንደሆነ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ በብልጽግና ፓርቲ እና በመንግስት ደረጃ በነበሩ ውይይቶች ላይ የአማራ ክልል ውሳኔ አሻራ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በስምምነቱ የተካተቱ ነጥቦች ተግባራዊ መደረጋቸው የአማራ ክልልN የሚጠቅሙ እንጂ በፍጹም የሚጎዱ አይደሉም ብለዋል።

የፖለቲካ ቁማርተኞች የአማራ ክልል በፕሪቶሪያው ስምምነት ተሳትፎ አላደረገምና ተጠቃሚ አልሆነም እያሉ የሚያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛና የተዛባ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ አንጻራዊ ሰላም፣ የተሻለ ልማት እና እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ደረጃ መታየቱንና በዚህም የአማራ ክልል ተጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም