ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በተግባር ያሳየ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት ሀገሪቱ የምትከተለውን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በተግባር የሚያሳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ከተማ ባካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የጎረቤትና የሌሎች አፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የዳያስፖራ ተወካዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኗን የሚያሳይ ነው።


 

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በንግግር እና በመግለጫዎች ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ በተግባር ቁርጠኝነቷን የምታሳይበት ሂደት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነትን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታትና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች ኢትዮጵያን በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ቀዳሚ ሀገር እንድትሆን ማስቻላቸውን ገልጸዋል።

ችግኝ ተከላው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየችበት መሆኑን በመግለጽ፤ ለቀጠናችንና ለአህጉራችን ለተሻለ የወደፊት ጊዜ፣ ለሰላምና ለአብሮነት ተስፋን እንተክላለን ብለዋል።

ከሱዳን፣ ከኬንያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቶች ጋር በጋራ የተካሄደው የችግኝ ተከላ ልምድን በማካፈል ቀጣናዊ ትስስርንና ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ሲያድጉና ሲያፈሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኙ ጠቁመው፤ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር እንዲጸድቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ፤ የዳያስፖራ አባላት በመርሃ ግብሩ በአካል በመገኘት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬቶች በተጨባጭ እንዲመለከቱ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ይህ ተሳትፏቸው በቀጣይ ሀገራዊ ጥረቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ድጋፍ ለማሰባሰብ ለሚደረገው ሥራ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል።


 

በኢትዮጵያ የናሚቢያ አምባሳደር ባፒዮ ምባውንጋ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሰጠችውን ተግባራዊ ምላሽ በማየታቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የደን ልማትን ማስፋፋታቸው የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅና የዓለም ሙቀትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ይህ ሌሎች ሀገራትም ሊቀስሙት የሚገባ ተሞክሮ ነው ብለዋል።

ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡት የዳያስፖራ አባል ዳዊት ዳተሞ፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሀገር አልፎ ለመላው ዓለም የሚተርፍ አዎንታዊ የአየር ንብረት ዘላቂነትን የሚፈጥር ዓለም አቀፋዊ በጎ ተጽዕኖ ያለው ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከአውስትራሊያ የመጡት ፓስተር ፖች፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መላውን ሕዝብ በአንድነት ያስተሳሰረ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ጥረት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የላቀና ኩራት የተሞላበት ሀገራዊ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም