ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ አስፈላጊ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በመጪው ሰኞ ለሚካሔደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሦስት ሺህ 554 የተከላ ቦታዎች ተለይተዋል።

የመትከያ ቦታዎች በጂፒኤስ (GPS) ቴክኖሎጂ በመታገዝ መለየታቸውን ጠቁመው የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠትም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ሪፖርት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በመርሃ ግብሩ የችግኝ መትከል ተግባሩን የሚያስተባብሩ ከአራት ሺህ በላይ ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል መመደቡን ገልጸዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ ሰኞ ማለዳ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በነቂስ በመውጣት አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለሰብል ምርታማነት ዕድገትና ለመስኖ ልማት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም