በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የቆዩና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የመጠጥ ውሃ ሽፋንና ተደራሽነትን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የቆዩና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የመጠጥ ውሃ ሽፋንና ተደራሽነትን ማሳደግ ተችሏል
አዳማ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የቆዩና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንና ተደራሽነትን ማሳደግ መቻሉን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ ።
በበጀት ዓመቱ ከ2 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
ቢሮው ከባለድርሻ አካላትና የዘርፉ አመራሮች ጋር በ2018 ዓ/ም በጀት ዓመት አፈጻጸምና በአዲሱ በጀት ዓመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩም የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የቆዩና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንና ተደራሽነትን ማሳደግ ተችሏል።
በተለይም ለዓመታት የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ምንጭ የነበሩ እንደ ሞጆ-አዳማ፣ ሳጉሬ-አሰላ፣ ቦረና፣ ወሊሶ እና አጋሮ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በበጀት ዓመቱ 2 ሺህ 300 የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከ4 ሺህ በላይ የኤሌክትሮ-መካኒካል ጥገናዎች በመደረጋቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ኢንጂነር ሚሊዮን አክለው እንደገለጹት፤ በየደረጃው የዲጂታል አሰራርና የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት የውሃና ፍሳሽ ተቋማት በሚያመነጩት ገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በአዲሱ የበጀት ዓመትም አገልግሎቱን በማዘመን የሀብት ብክነትን በመቀነስ ተቋማቱ ተጨማሪ ገቢ የሚያመነጩበትን አሰራር በመዘርጋትና በገቢ ራስን ማስቻል ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የምዕራብ ሐረርጌ ውሃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሾ ዴከሞ፤ በዞኑ 8 ትላልቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው 69 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አክለውም በነዳጅ ይሰሩ የነበሩ የውሃ ተቋማትን ወደ ኤሌክትሪክና ፀሐይ (ሶላር) ኃይል የመቀየር ሥራ መከናወኑንና አዳዲስ ፕሮጀክቶችም በዚህ አሰራር እየተገነቡ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
የምዕራብ ሸዋ ውሃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ታፈሰ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ 154 የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ ከ100 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት የዞኑ የውሃ ሽፋን ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።