በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በያዝነው ዓመትም ተጨማሪ 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መላው ኢትዮጵያውያን የፊታችን ሰኞ በአንድ ክንድ ተባብረው፣ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ እንዲጽፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህንኑ ጥሪ ተከተሎ ኢዜአ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የነዋሪዎችን ዝግጁነት ጠይቋል።
ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ምህረቱ በቀለ እንደገለጸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገርን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በተለይም የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመቀነስና የከተማዋን ውበት በመጨመር በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ በዕለቱ አሻራውን ለማኖር ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል።
ወይዘሮ ተስፋነሽ ከፈነ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሀገሪቱ ከተጀመረ አንስቶ በየዓመቱ አሻራቸውን ሲያሳርፉ መቆየታቸውንና የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይም ከነቤተሰባቸው ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታሲስ ጋዲሳ በበኩላቸው፤ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ናቸው ያለው ደግሞ አቶ ዮሐንስ ደሳለኝ ነው።
የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ በከፍተኛ ጉጉት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ወጣት ዳግም አዲስ በበኩሉ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መሳተፍ ለሀገርና ለትውልድ ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ፣ በዕለቱ የሚኖረውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ቀኑን በጉጉት እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡