ቀጥታ፡

የወርሀ ሰኔ እና ሐምሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁልፍ ተግባራት ቅኝት

ሀገራዊ ምክክር:-

‎የሀገራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን በዚህ ሥነስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክን ለመጻፍ የሚያስችላትን ብዕርና ብራና ያገኘችበት አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው፤ ተሳታፊዎች ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል። ከሶስት እስከ አራት ተከታታይ ሳምንታት የሚደረገው ይህ ሀገራዊ ምክክር የሀገሪቱን ብዝሃነት የሚወክሉ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን የያዘ ሲሆን፤ ተሳታፊዎቹም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አሳትፎ ከሥር ወደ ላይ በዘለቀ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተመሰረቱ ስምንት ስትራቴጂካዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀትና ሀገርን ባስቀደመ መልኩ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

የፕሮጀክቶች ጉብኝትና ምረቃ:-

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደብረ ማርቆስና አካባቢው ህዝብ ለዓመታት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውንና ለ30 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የአውሮፕላን ማረፊያ በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ መርቀው ከፍተዋል። የዚህ ፕሮጀክት ምርቃት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መጀመር በቻ ሳይሆን በአግባቡ በጥራትና በፍጥነት የመጨረስ ባህልን እያዳበረች እንደሆነ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወርኃ ነሐሴ 2017 ዓ.ም በጋሞ ዞን ሥራ ጀምሮ የነበረውን ‘ዮ ሆልዲንግ’ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ አሁናዊ ሁኔታ ጎብኝተው የተደረሰበትን የስራ አፈጻጸም አበረታተዋል።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነው ዘመናዊው ሀማሳ ሞዴል መንደር መርቀው በይፋ የከፈቱ ሲሆን በተጨማሪም በአርባ ምንጭ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ የጫኖ ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን የግንባታ ሂደት እና በአርባ ምንጭ የተገነባውን የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓን ጎብኝተዋል። የገበታ ለትውልድ መርሃ-ግብር ፍሬ የሆነውንና በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንትን ያካተተውን የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትም በይፋ መርቀዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ:-

‎በ2018 ዓ.ም የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር መጠነ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገበት እንደሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህም ዓመት 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እንደታቀደ ገልጸው መላው ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ታሪክን እንዲሰሩና በጋራ ተስፋን እንዲተክሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የዘንድሮው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሀግብር ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነት:-

‎በተያዘው የሐምሌ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሀገራትና አህጉራዊ ተቋማት መሪዎች ጋር ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፤ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ፣ ከቤኒኑ ፕሬዝዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ እና ከአዘርባጃን ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ ጋር በሁለትዮሽ፣ ስትራቴጂካዊና አዳዲስ የትብብር መስኮች ላይ ሲመክሩ፤ ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ካጃ ካላስ ጋር ደግሞ በአፍሪካ-አውሮፓ ግንኙነት፣ ቀጣናዊ ጉዳዮችና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማሳደግ ዙሪያ ተወያይተዋል። በተጨማሪም ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጋር በሀገራዊ ምክክርና በሰላም ግንባታ ልምድ የተለዋወጡ ሲሆን፣ ከአፍሪ ኤክሲም ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጆርጅ ኤሎምቢ እና ከባንኩ የቦርድ አባላት ጋር አህጉራዊ አጋርነትንና የዕድገት ዕድሎችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኳታር አቅንተው በቀድሞው የኳታር አሚር ሼክ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ታኒ ሕልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን የገለጹ ሲሆን ለቤተሰባቸውና መላ ህዝባቸው መጽናናትን ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ አጋርነትን አመላክተዋል።

ማኅበራዊ ጉዳይ:-

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ተኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት የመንግሥትን አፈጻጸም እና የቀጣይ እቅዶችን አብራርተዋል። የምክር ቤቱን አባላት የ5ዓመታት አገልግሎት ዘመን ማጠቃለያን በማስመልከት በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ስም ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል። በተያያዘም በሐምሌ ወር ማገባደጃ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች ዙሪያ ቃለ-መጠይቅ ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ታሪክ እንደሚያስረዳን፣ ከራስ ጥቅም ወጥተን በጠንካራ መደጋገፍ ለጋራ ልማት፣ ለሀገር ህልውና፣ ለህዝቡ ሰላምና የኑሮ መሻሻል መትጋት እንደሚገባ አመላክተዋል።

#PMOEthiopia

#EthiopiaDelivers

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም