ቀጥታ፡

በክልሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሀ-ግብር የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

ሐረሪ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።

በመድረኩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ ዐሻራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት በክረምት በጎ ፈቃድ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።

በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሀ-ግብር ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

በተለይ የሴፍቲኔት ተረጂዎችን በሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብሮች ተጠቃሚ በማድረግ ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተረጂነትን ለመቀነስ ይሰራል ነው ያሉት።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ልማት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በክልሉ በተለያዩ 14 ቦታዎች ላይ በአንድ ጀንበር ችግኝ ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮና የማጓጓዝ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች ለሚከናወነው ይህ መርሃ ግብር ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ ግንዛቤ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

በመርሃ -ግብሩ የክልሉ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ አመራርና አባላት እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ የክልሉ የጸጥታ ኃይል አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም