ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ አስተዳደሮች በ2018 በጀት ዓመት በጸጥታና ህግ ማስከበር በቅንጅት ያከናወኗቸው ተግባራት አመርቂ ውጤት አስገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ አስተዳደሮች በ2018 በጀት ዓመት በጸጥታና ህግ ማስከበር በቅንጅት ያከናወኗቸው ተግባራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸው ተመላከተ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የሸገር ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ጽሕፈት ቤት በ2018 በጀት ዓመት የጋራ የጸጥታ ሥራ አፈጻጸም እንዲሁም በ2019 በጀት ዓመት የጋራ ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በጸጥታ ዘርፍ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ቀደም ሲል ስምምነት አድርገዋል ብለዋል።


 

ይህንኑ ስምምነት መነሻ በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የጋራ የሰላምና ጸጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በተከናወነው የተቀናጀ ስራና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የወንጀል መከላከል ሥራ፣ የወንጀል መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ጠቁመው፤ ይህ አዎንታዊ ትብብር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ከተሞች በጋራ ባቀዱት መሠረት በተለይም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማክሸፍ በኩል ስኬታማ ሥራ ሰርተዋል ብለዋል።

በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ያሉ የጸጥታ ኃይሎችን በማቀናጀት፣ የጋራ ዕቅድና መመሪያ በማዘጋጀት የጸጥታ ስጋቶችን በቅድመ-መከላከል ማክሸፍ መቻሉን ጠቁመዋል።

አክለውም በ2018 ዓ.ም የተከናወኑ የተቀናጁ የፀጥታ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ጠቁመው ቅንጅቱ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሮቹ በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ፣ በ2019 በጀት ዓመት የላቁ ተግባራትን በጋራ ማከናወን የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም