በአዳማ ከተማ የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ተግባራትን ማከናወን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ተግባራትን ማከናወን ተችሏል
አዳማ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ተግባራትን ማከናወን መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ ገለጹ።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት፣ ክፍለ ከተሞችና የልማት አጋሮች የማበረታቻ ዕውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ገቢ በማሳደግና የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የከተማዋን ዕድገት የሚያሳልጡ በርካታ የልማት ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
በተለይ የታክስ ሥርዓቱን መልክ በማስያዝ በተከናወኑ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ ከዕቅድ በላይ 20 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በቤቶች ልማት፣ በመሬት አስተዳደርና በመሠረተ ልማት ግንባታም ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ አገልግሎቶችን በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ዕድገቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ዕውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል የአዳማ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላቸው አሰፋ ዕውቅናው በቀጣይ ይበልጥ ለመሥራት እንደሚያነሳሳቸውና ውጤቱም በመላ ተቋሙ ሠራተኞች ጥረት የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የደካ-አዲ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ኃይሌ ሂርጶ በበኩላቸው አስተዳደሩ ባከናወናቸው ሰው ተኮር የልማት ተግባራት የመኖሪያ ቤትና ተያያዥ ችግሮችን በመፍታት የሕዝቡን ፍላጎት ለማርካት በትጋት መስራቱን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።
ዕውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል የከተማዋ ገቢዎች፣ ግብርና፣ ማዘጋጃ ቤት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የመሬት አስተዳደር ሴክተሮች በአፈጻጸማቸው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ የወጡ ሲሆን፤ ለከተማዋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሀብቶችና ድርጅቶችም ዕውቅና ተሰጥቷል።