በጋምቤላ ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተደርጓል
ጋምቤላ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ለመመለስና የደን ሽፋንን ለማሳደግ በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትልቅ እመርታዊ ለውጥ አምጥቷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም «ተስፋን እንትከል!» በሚል መሪ ሐሳብ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከልም ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።
ይህንኑ ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በጋምቤላ ክልልም የመትከያ ስፍራዎችን የመለየት፣ የጉድጓድ ዝግጅትና የችግኝ ማጓጓዝ ሥራዎች ተጠናቀቀው የዕለቱን መርሃ ግብር በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።
በዚህም በዕለቱ በጋምቤላ ክልል በ17 የተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱ መጠናቀቁን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ ገልጸዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች የዚሁ ሀገራዊ ሁነት ታሪክ አካል ለመሆን መዘጋጀታቸውን አንስተው በዕለቱ በመውጣት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚሁ መርሃ ግብር ችግኞች የሚተከሉበት ከ330 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ለደን ልማትና ለአካባቢ ውበትና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።