ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያችሉትን ተግባራት እያከናወነ ነው

ሀረር፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሐረሪ ሪጅን ጽህፈት ቤት ዘመናዊ ህንጻ ግንባታ ማስጀመርያ ስነ ስርዓት አካሂዷል።

በግንባታ ማስጀመሪያው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ ለምለም ምስጋናው፣ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብርጋድየር ጀነራል ኢንጂነር ሰጠኝ ሊኪሳ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ለምለም ምስጋናው በወቅቱ እንደገለጹት ተቋሙ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ ነው ።

ለዚህም የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው በሐረሪ ክልል የሚገነባው ህንጻም የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን አመላክተዋል።

አዲስ የሚገነባው የሐረሪ ሪጅን ጽህፈት ቤትም 10 ወለሎች ያሉትና 2 ቢሊየን በሚጠጋ ብር የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል ።

የግንባታ ስራው በ900 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ግንባታውን እንደሚያከናውንም አስታውቀዋል።

የህንጻው መገንባት በሪጅኑ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል ያስችለዋል ያሉት ደግሞ የአገልግሎትቱ የሐረሪ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሪክተር አቶ ካሊድ ጠሃ ናቸው።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብርጋድየር ጀነራል ኢንጂነር ሰጠኝ ሊኪሳ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ በሀገሪቱ በርካታ የህንጻ፣ የመንገድና ሌሎች ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሐረሪ ሪጅን ጽህፈት ቤት ዘመናዊ ህንጻ ግንባታንም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በፍጥነትና በጥራት እንደሚያከናውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም