ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማዕከል አድርገዋታል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ሀገሪቷን ተመራጭ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንዳደረጓት የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የህንድና የፊንላንድ አምባሳደሮች ገለጹ።

አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን ጨምሮ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እያከናወነቻቸው ያሉትን እርምጃዎች አድንቀዋል።

የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ቀጣይነት ያላቸው ሪፎርሞች እና ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሀገሪቱን ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ እያደረጓት መሆኑን ገልጸዋል።

በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፈጣን የከተሞች ለውጥ እና ትላልቅ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሟን የሚያሳድጉ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን ጨምሮ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማስፋት ያከናወነቻቸው ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ነው አምባሳደሩ የጠቀሱት።

ለአብነትም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፎች በኢትዮጵያ ትልቅ አቅም መፈጠሩንም አመልክተው፤ ሪፎርሙን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር የህንድ ኩባንያዎችን እየሳበ መሆኑንም አስረድተዋል።

አዳዲስ የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እየተጫወተች ያለችውን ሚናም አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እና የሕዝቡ ተሳትፎ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ስኬታማ ጉዞ ያንጸባረቀ መሆኑን አመልክተው፤ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክርም ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

ሂደቱ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን እየፈታች ብሔራዊ አንድነቷን ለማስጠበቅ እና የልማት ጎዳናዋን ለማስቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በየዘርፉ እየታየ ያለው ለውጥ አስደማሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ፊንላንድና ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በፈጠራ ሥራዎች እና በቴክኖሎጂ ትብብራቸውን ለማጠናከር ሰፋፊ ዕድሎች እንዳሏቸው አብራርተው፤ በልማት ትብብር በጋራ መሥራታቸውንም ይቀጥላሉ ብለዋል።

ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ እና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ኢንቨስትመንቶች ላይ ያላትን አጋርነት እንደምታጠናክርም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም