ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገለፀ።

የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንስቲትዩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገቡ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችንና የወደፊት እቅዶችን በሆሳዕና ከተማ እያገመገመ ነው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ እንደተናገሩት፤ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።


 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ በመደገፍ በኩል ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አስተማማኝና ዘላቂ የኢኮኖሚ መሰረት ከማድረግ ባለፈ ለስራ ፈጠራ እንዲውል እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅትም የቱሪስት መስሕቦችን የማደስ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት ስራ መከናወኑ የኢትዮጵያን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭነት እያሳደገ ነው ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኚዎች እንዲሁም ከ 50 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የተለያዩ መስሕቦችን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ሙያዎች ዜጎችን ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ በማሰልጠንና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በሆሳዕና ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሔደ ባለው የምክክር መድረክ የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም