የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት አስጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር “6400 A” የተሰኘ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) ገቢ የሚሰበስብበት አዲስ የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት በይፋ አስጀምሯል።
በመርሐግብሩ ማስጀመሪያ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዣንጥራር አባይ፤ በመዲናዋ በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በጎ ፈቃደኞች የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በተለይም በደም ልገሳ፣ ለአረጋውያንና አቅመ-ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ በትምህርትና በአካባቢ ልማትና በሌሎችም ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የበጎ ፈቃድና የማኅበረሰብ ልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመጠቆም።
የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለማዘመንና ለማጠናከር የተዘረጋውን የዲጂታል አማራጭ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በስፋት እንዲጠቀሙበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ፕላትፎርሙ ዋና ዓላማ ከበጎ ፈቃደኞች በቀን 1 ብር ወይም በወር 30 ብር በመሰብሰብ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊየን አባላትን በማፍራት ከ360 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ የታቀደ መሆኑን አስረድተዋል።
የሚሰበሰበው ገቢ የአቅመ-ደካሞችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚያቃልሉ ዘላቂ ፕሮጀክቶች ላይ ይውላል ብለዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት የዛሬው መዋጮ ለነገ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መሠረት ነው፤ ፕሮጀክቱ ገንዘብ ከማሰባሰብ ባሻገር የራስን ችግር በራስ የመፍታት ባህልን ማሳደግና ወጣቶችን የበጎ አድራጎት አምባሳደር ማድረግን ያለመ ነው ሲሉም ገልጸዋል።