የአማራ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ በጀት ዓመት ከ402 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ በጀት ዓመት ከ402 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መርምሮ አጸደቀ
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ምክር ቤት በ2019 በጀት ዓመት ለሚካሔዱ የልማት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ402 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መርምሮ አጽድቋል።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በሦስተኛ ቀን ውሎው በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር እና የአዲሱነ በጀት ዓመት የዕቅድ ማስፈጸሚያ በጀት በማጽደቅ ተጠናቋል።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አታላይ ጥላሁን የበጀት ረቂቁን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ በጀቱ የክልሉን ህዝብ የመልማት ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው።
ከበጀቱ ውስጥ ከ286 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን 111 ቢሊየን የሚጠጋው ደግሞ ከፌደራል መንግስት ጥቅል የቀመር መደበኛ ድጋፍ የሚገኝ ነው ብለዋል።
ቀሪው ከዘላቂ ልማት ግቦችና መሰል የፋይናንስ ምንጮች በሚገኝ ሀብት የሚሸፈን እንደሆነም ተናግረዋል።
የበጀት ድልድሉ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦችን፣ የመዋቅር ማሻሻያዎችን፣ ብሎም ወረዳዎችና ከተሞች የድህነት ተኮር ዘርፍ ያለባቸውን የካፒታል በጀት ውስንነት መሰረት የተደረገ ነው ብለዋል።
የተመደበው በጀት ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ176 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ወይም 78 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
በጀቱ የክልሉን ህዝብ የላቀ የልማት ጥያቄ ፍላጎት መሰረት በማድረግ የቀረበ እንደሆነም አብራርተዋል።
የቀረበውን በጀት የህዝብን የልማት ጥያቄ በአግባቡ ሊመልስ በሚችል አግባብ ለታለመለት ዓላማ በቁጠባ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለስኬታማነቱም በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።