የልብ በሽታን መከላከል የሚያስችል የሕክምና አቅምን የመገንባት ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የልብ በሽታን መከላከል የሚያስችል የሕክምና አቅምን የመገንባት ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት የልብ በሽታን መከላከል የሚያስችል የሕክምና አቅምን ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር (ESCP) እና የፓን-አፍሪካ የልብ ሕክምና ማኅበር (PASCAR) በጋራ ያዘጋጁት "የESCP–PASCAR ኮንግረስ 2026" ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባኤው በአፍሪካ የልብና የደም ሥር ጤናን ለማጠናከር፣ ሳይንሳዊ እውቀትን ለመለዋወጥና የባለሙያዎችን ትብብር ለማጎልበት ያለመ ነው።
በመድረኩ ጤና ሚኒስቴርን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ፤ የልብና ደም ሥር በሽታዎች ለሰው ልጅ ሞት ምክንያት ከሆኑ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ዋናው ነው ብለዋል።
ሕመሙን በቅድመ-ምርመራ እና በጊዜው በሚገኝ ጥራት ያለው ሕክምና መከላከል የሚቻል ቢሆንም፣ አሁንም ሰፊ የቤት ሥራ በመኖሩ ምክንያት አምራች የሰው ኃይልን እያሳጣ ይገኛል ነው ያሉት።
የበሽታውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ቅድመ-ምርመራን፣ ድንገተኛና ልዩ ሕክምናዎችን፣ ማገገሚያዎችን እንዲሁም ምርምርና ፈጠራን ያካተተ ጠንካራ የጤና ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ጉባኤው የአፍሪካውያንን የተቀናጀ ሥራ ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚሁ ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው በመሠረታዊ የጤና እንክብካቤ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ ልዩ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠናን በመጨመር፣ በከፍተኛ ሕክምና ማዕከላት ማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በሽታዎችን በመከላከል፣ አስፈላጊ መድኃኒቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ በኩል ከሙያ ማኅበራት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከልማት አጋሮችና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ናትናኤል ታዬ፤ የሕክምና መገልገያዎች እጥረት፣ የአገልግሎት አለመዳረስ እና የወረፋ ጥበቃ በዘርፉ ዋና ዋና ፈተናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም እነዚህን ፈተናዎች በመቋቋም ልዩ የሕክምና አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥ ሥልጠናና ምርምርን ማጠናከር፣ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂዎችን መተግበርና ዘርፉን የሚቀይሩ አጋርነቶችን የመገንባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፓን-አፍሪካ የልብ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሀቢብ ጋምራ፤ በሽታውን ለመከላከል የሙያተኞች የእውቀትና ልምድ ልውውጥ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉባኤው የጋራ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ይረዳል ብለዋል።