ቀጥታ፡

የዛሬ ችግኞች የነገ የሀገር ትሩፋቶች 

የኢትጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከተሰጡ ሀገር በቀል ምላሾች መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

መርሃ ግብሩ ሀገር በቀል እውቀት፣ የጋራ ተግባር እና መጠነ ሰፊ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማቀናጀት ስኬታማ የሆነ ለዓለም የሚደርስና ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማበጀት እንደሚቻል በተግባር የሚያሳይ ነው።

አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ትሩፋቶቹ፣ የተራቆተ መሬትን እንዲያገግም ከማድረግ፣ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመጨመር እና የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አንጻር ካለው ፋይዳ ባሻገር አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮት ከውጭ መፍትሄ እስኪመጣ ከመጠበቅ በራሷ አቅም መፍትሄን ማመንጨት እንደምትችል በተግባር አሳይቷል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ግብ ችግኝ መትከልና የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ግንባታ፣ የህዝብ አንድነትና የኢኮኖሚ ልማት ማዕከል ማድረግ ሲሆን ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉና ለጋራ ብልጽግና በጋራ እንዲሰሩ እድል የፈጠረ ህዝባዊ ንቅናቄም ጭምር እንጂ።

ይህን ሀገራዊ መርሃ ግብር ይበልጥ ለማጠናከር “ተስፋን እንትከል!” በሚል መሪ ሀሳብ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አማካኝነት በይፋ ተጀምሯል።

በዚህ ዓመት ብቻ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያዊያንን የማድረግ አቅም የሚያሳይ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ነው።

በተከታታይ በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ስራም በ2010 ዓ.ም. 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን 2016 ዓ.ም. ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ ሊደርስ ችሏል።

ለበርካታ አስርት ዓመታት የቆየውን የመሬት መራቆት መግታትም ተችሏል። በተጨማሪም ይህ ኢኒሼቲቭ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ፋይዳ ግን የአፈርና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም የደን ሽፋን መጨመር ብቻ አይደለም፤ የተፈጥሮ ደኖች መስፋፋታቸው ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የማር ምርትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግና የስርዓተ-ምግብ መሻሻል እንዲረጋገጥ አድርጓል።

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያውያን ክንድ ተባብሮ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቀጠሮ ተይዟል። 

ይህ ታሪካዊ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላውን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት  ውድ የሀገሬ ልጆች፤ በእነዚህ ቀናት አስፈላጊውን ዝግጅት እንድታደርጉ፣ በቁርጠኝነት እንድትነሱ እና በአንድነታችን የምናስመዘግበውን ድል እውን እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በጋራ ተስፋን እንትከል!  ብለዋል። 

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ፣ ዛፎችን የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የተስፋ፣ የህብረት እና የሀገራዊ ህዳሴ ምልክት ነው። 

የዛሬዎቹ ችግኞች የነገዎቹ ደኖች፣ የነገዎቹ የውሃ ምንጮች እና የነገው ትውልድ ንጹህ አየር ናቸው። 

ይህ ንቅናቄ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳየችበት፣ ዜጎቿም ለሀገራቸው እድገት በጋራ ሲቆሙ ምን ያህል ታላቅ ነገር መስራት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

ዛሬ የተተከለው እያንዳንዱ ችግኝ ለነገዋ አረንጓዴ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚቀመጥ ጠንካራ የማዕዘን ድንጋይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም