የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በተግባር ያሳየ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በተግባር ያሳየ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት ሀገሪቱ የምትከተለውን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በተግባር የሚያሳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ የጎረቤትና የሌሎች አፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኗን ማሳያ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስተዋወቅን ጨምሮ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ሀገሪቱን በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ቀዳሚ ማድረጋቸውንም አብራርተዋል።
ችግኝ ተከላው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየችበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለቀጣናችንና ለአህጉራችን ለተሻለ የወደፊት ጊዜ፣ ለሰላምና ለአብሮነት ተስፋን እንተክላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ከሱዳን፣ ከኬንያ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቶች ጋር የተካሄደው የችግኝ ተከላ ልምድን ለማካፈል፣ ቀጣናዊ ትስስርንና ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የሚተከሉት ችግኞች ሲያድጉና ሲያፈሩ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እንዲጸድቁና የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጡ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።