ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

ወላይታ ሶዶ ፤ ሐምሌ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ከ6 ሺህ 450 ሄክታር በላይ መሬት ላይ እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ (ዶ/ር) በዞኑ ለዘንድሮ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ለመርሃ ግብሩ በተለዩ የመትከያ ቦታዎች ኅብረተሰቡን በንቃት ለማሳተፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩም የፍራፍሬ፣ የቀርከሃ፣ የውበትና ጥላ፣ የጥምር ደን እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ከ6 ሺህ 450 ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል ብለዋል።
 
ለዚህም የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በሙሉ መጠናቀቁን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በዕለቱ ከ828 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ለዘመቻው መሳካትም በሳይንሳዊ ዘዴ የመትከያ ቦታዎች ልየታ መደረጉን በመጠቆም ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጥሪ አቅርበዋል።

«የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከተጀመረ ወዲህ ገላጣ የነበሩ መሬቶች ለምተውና የደረቁ ምንጮች በመፍለቃቸው አርሰንም ሆነ አርብተን የተሻለ ኑሮ መምራት ጀምረናል» ያሉት ደግሞ በዞኑ ዳሞት ጋሌ ወረዳ የሻኪሾ ሾኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገላነህ ቱማቶ ናቸው።

ከዚህም የተነሳ ክረምቱ ከገባ ጀምሮ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች መትከል መጀመራቸውን አንስተው ሰኞ ዕለት ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር ተከላም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው የቡጌ ቀበሌ አርሶ አደር ነጋ ጌቶ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የተከሏቸው የፍራፍሬ እና ሌሎች ችግኞች ደርሰው በመሸጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ያነሳሉ።

ዘንድሮም ከ100 በላይ ችግኞችን ለመትከል በግብርና ባለሙያ ድጋፍና ትምህርት መሠረት የጉድጓድ ቁፋሮ ማከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም